(Translated by https://www.hiragana.jp/)
ውክፔዲያ - ሰምሳረ Jump to content

ሰምሳረ

ከውክፔዲያ

ሰምሳረ (ሳንስክሪት संसार፣ «መዛወር») ከሕንድ አገር በወጡት ሃይማኖቶች የ«ተመላሽ ትስብዕት» ትምህርት ማለት ነው፤ የሞቱት ነፍሶች ተመልሰው ዳግመኛ ከማሕጸን ይወለዳሉ የሚል እምነት ነው። ይህ ሀሣብ በሂንዱኢዝም እና በቡዲስም እንዲሁም በጃይኒስምና በሲኪስም መሠረታዊ ነው።

የሰምሳረ ሀሣብ በታሪክ ገጽ በሰነዶችም መጀመርያ ሲታይ (800-700 ዓክልበ. ግድም)፣ እንደ ፍልስፍና ግመት፣ አንድምታ ወይም እንደ ሃልዮ ቀረበ፣ እንጂ ይህ ከእግዚአብሔር እንደ ተገለጸ እርግጥኛ ትምህርት ነው የሚል እንደ ነበር አይመስልም። በኋላ ሀሣቡ በሕንድ ተቀብሎ ጸንቶ ቀስ በቀስ ከአንድምታ ወደ ጸና ትምህርት መሠረት ተለወጠ። ከጎታማ ቡዳ ዘመን (600-500 ዓክልበ. ግድም) በፊት፣ በሕንድ ውስጥ የማይጠያየቅ የፍልስፍና መሠረት ሆኖ ነበር፤ ነፍሶች በትክክል ወዴት እንደሚሄዱ ለምን ያሕል ጊዜ ለማወቅ ከሰማይ ወይም ከመንፈሶች ለመማር እንደ ተቻላቸው ብለው መናገርንና መጻፍን ደፈሩ። እያንዳንዱ ሃይማኖት ወይም ፍልስፍና ግን በተገለጹት ዘዴዎች ዝርዝር ይለያያሉ።

በ«አብርሃማዊ ሃይማኖቶች» (አይሁድናክርስትናእስልምና) ግን የሙታን ትንሳኤዕለተ ደይን ትንቢቶች ስላሉ፣ ተምላሽ-ትስብዕት ለተራ ሰዎች አለመቻሉ ይታመናል። በብሉይ ኪዳንትንቢተ ሚልክያስ 4:5 «ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ» ስላለው፣ ለቅዱስ ኤልያስ ተመላሽ ትስብዕት እንደ ተፈቀደ የሚያምኑ አሉ። እንዲሁም በአዲስ ኪዳን የማቴዎስ ወንጌል 11:14 ኢየሱስ ስለ ዮሐንስ መጥምቁ «ልትቀበሉትስ ብትወዱ፣ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው» ስላለ፣ ኤልያስ እንደ ዮሐንስ ተመለሰ የሚያስተምሩ ጥቂቶች (በተለይም ኖስቲሲስም) ናቸው። ነገር ግን የዮሐንስ ወንጌል 1:21 ዮሐንስ በግልጽ «ኤልያስ አይደለሁም» አለ፤ የሉቃስ ወንጌል 1:17 ደግሞ ዮሐንስ «በኤልያስ መንፈስና ኃይል» እንደሚሄድ ይላል እንጂ የኤልያስ ነፍስ አይልም፣ በተጨማሪ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ላይ ኤልያስንም ሙሴንም በተዓምር በትንሳኤ እንጂ በልደት አላመጣቸውም፤ ስለዚህ ሁሉ በአጠቃላይ ኤልያስ እራሱ እንደ ዮሐንስ አልተመለስም ይታመናል።