ታክሲላ
ታክሲላ ተክሸሺላ፣ ተከሺላ | |
---|---|
ታላቅ ቁልል | |
ሥፍራ | |
መንግሥት | ገንዳረ፣ ፋርስ፣ ሕንድ፣ ባክትርያ፣ ኩሻን መንግሥት፣ ጉፕታ መንግሥት |
ዘመን | 1000 ዓክልበ. - 460 አም |
ዘመናዊ አገር | ፓኪስታን |
ጥንታዊ አገር | ገንዳረ |
ታክሲላ በአሁኑ ፓኪስታን የነበረ የጥንት ከተማ ነው።
ስሙ በሳንስክሪት ተክርሸ-ሺላ «የተቆረጠ ድንጋይ» ነበረ፣ በፓሊኛ ተከሺላ ሆነ። ይህም በኋላ በግሪክኛ «ታክሲላ» ሆነ።
ከተማው በ1000 ዓክልበ. ያህል እንደ ተመሠረተ ይታስባል። የንግድ ማዕከልና የገንዳረ መንግሥት ዋና ከተማ ሆነ። ከተማው በሂንዱኢዝም፣ ቡዲስምና ጃይኒስም አፈ ታሪክ ይገኛል።
የታክሲላ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ልክ መቼ እንደ ተመሠረተ አይታውቅም፣ ግን ከጎታማ ቡዳ ዘመን (500 አክልበ. ግድም) በኋላ የቡዲስም ትምህርት ተቋም እንደ ሆነ ይመስላል። ይህም ተቋም ስንኳ ከፕላቶ አካዳሚ በፊት በመሆኑ ምናልባት የዓለሙ መጀመርያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሊባል ይችላል።
በተቋሙ ውስጥ ከተማሩት ጥናቶች መካከል፦ ቬዳዎቹ፣ ቀስትን ማስፈንጠር፣ የጦር ሠልፍ፣ ማደን፣ የዝሆን ወግ፣ ሕግና ሕክምና ነበሩ። ተማሪ በአስራ ስድስት አመት እድሜ ይጀመር ነበር፣ ከመላው ሕንድ አገር ተጓዝተው ይደርሱ ነበር። ለተማሮች ገንዘብን አላስከፈሉም፣ ድሆች የሆኑትም በምሽቱ፣ ባለሀብቶችም በቀን ይማሩ ነበር። ትምህርቱ አስተማሪው እስከሚጨርስ ድረስ ቀጠለ፣ እንጂ እንደ ዘመናዊ ዩኒቨርስቲ ስርዓት ፋከልቲ አዳራሽ ወይም ዶርሚቶሪዎች ወይም የተወሰነ ጊዜ ወይም ዲግሪ አልነበረም። የማንም መንግሥት አስተዳደር አልነበረውም፤ ከሀብታም ዜጎች ግን የልግሥና ድጋፍ ይቀበሉ ነበር።
በታክሲላ ተቋም ታዋቂ ከሆኑት ተማሮች መካከል፦
- ቸረከ 800-500 ዓክልበ. ?- የአዩርቬዳ (የሕንድ ባሕላዊ ሕክምና) ደራሲ
- ጂቨከ 500 ዓክልበ. ግድም - የማጋዳ ንጉሥ የቢምቢሳራ ሐኪም፣ በጎታማ ቡዳ ዘመን
- ፓሰናዲ 500 ዓክልበ. ግድም - የኮሳላ ገዥና የጎታማ ቡዳ ተከታይ
- ፓኒኒ 350 ዓክልበ. ግድም ? - የሳንስክሪት ስዋሰው ደራሲ
- ቻነክየ (ካውጢልያ) 320 ዓክልበ. ግድም - የሕንድ ፈላስፋ፣ የምጣኔ ሀብት ደራሲ
ከተማው በፋርስ ንጉሥ ፩ ዳርዮስ በ524 ዓክልበ. ተያዘ፣ የፋርስም ነገሥታት ለመቶ ዓመት ያህል ይገዙት ነበር።
በ334 ዓክልበ. ታላቁ እስክንድር ከተማውን ከንጉሡ አምቢ ያዘ። ግሪኮች ከተማው ሀብታምና በጥሩ አስተዳደር እንዳገኙት ጻፉ።
ከዚህ ትንሽ በኋላ የማውርያ መንግሥት (ሕንድ) ንጉሥ ቻንድራጉፕታ ያዘው። አማካሪው ቻነክየ ወይም ካውጢልያ ዝነኛ መጽሐፉን አርጠሻስትረ («የምጣኔ ሀብት ዕውቀት») የጻፈው በታክሲላ እንደ ነበር ይባላል። የቻንዳራጉፕታ ልጅ አሾካ በተለይ ቦታውን የቡዲስም ጥናት ማዕከል አደረገው።
በ180 ዓክልበ. የግሪኮች ባክትርያ መንግሥት ታክሲላን ያዙ። ከዚያም በ98 ዓክልበ ሳካዎች ያዙት። የገንዘብ (መሐለቅ) መሥሪያ ቤት በታክሲላ ነበራቸው።
በ28 ዓክልበ. ግድም የጳርቴ ሰዎች ወርረው ያዙት። የኢየሱስ ሐዋርያ የሆነው ቅዱስ ቶማስ በ38 ዓም ወደ ታክሲላ እንደ ደረሰ ይታመናል። ከዚያ በኋላ ወደ ሕንድ ሄዶ ወንጌልን እዚያም ሰበከ። የግሪክ ፈላስፋ አፖሎንዮስ ዘቱዋና ደግሞ በዚያው ወቅት ታክሲላን እንደ ጎበኘ ይባላል።
ከ68 ዓም በፊት ታክሲላ በኩሻን መንግሥት ተያዘ። ከ370 ዓም በኋላ የጉፕታ መንግሥት (ሕንድ) ያዘው። በዚህ ዘመን የሐር፣ ሰንደል፣ ፈረስ፣ ጥጥ፣ ብር፣ ሉል (ዕንቁ)ና ቅመም ንግድ ማዕከል ነበረ። የቻይና ተጓዥ ፋሥየን ታክሲላን በ400 ዓም ግድም ጎበኘ።
በ440 ዓም ኪዳራውያን (የሁኖች ወገን) ወርረው ጥቃት በታክሲላ ላይ ጣሉ። ከዚያ በኋላ በዙሪያው ጦርነት ይበዛ ነበር። በመጨረሻ በ460 ዓም ግድም ሄፕታላውያን ወይም «ነጭ ሁኖች» ቦታውን ትምህርት ቤቱንም አጠፉ።
የቻይና ተጓዥ ሥወንዛንግ ዙሪያውን በ630 ዓም በጎበኘው ጊዜ ከጥቂት መኖክሶች በቀር ፍርስራሽ ብቻ አገኘ።
ፍርስራሹ እንደገና በ1855 ዓም በሥነ ቅርስ ሊቆች ተገኘ።